Award Ceremony 2025


Journalist Kidist Belay

Journalist Kidist Belay

ስለ ጋዜጠኛ ቅድስት በላይ

ከአስራ አንድ ዓመታት አንስቶ ነዋሪነትዋን በራፐርስቪል-ዮና ከተማ ውስጥ በማድረግ የስዊዘርላንድን የስደተኛነት ሕይወት የተቀላቀለችው የዛሬዋ የእውቅና ባለቤት በሙያዋ ጋዜጠኛ ስትሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጆርናሊዝም ኤንድ ኮሚዩኒኬሽን በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቃለች። ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረችበትም ወቅት ከሙያዋ ባሻገር በተለያዩ የአመራር ሥራዎች በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሊቪዥን ድርጅት እንደሰራች የሕይወት ማህደሯ ያሳያል።

የሕይወት አጋጣሚ ሆኖ ከቅርብ ጊዜያት አንስቶ ቬትዚኮን ዙሪክ በሚገኘው ቤተ መጻህፍት ውስጥ ከጋዜጠኛነት ሙያዋና ልምዷ በተለየ ሁኔታ የላይብረሪያን ሥራ በመለማመድ አዲስ የህይወት ምዕራፍ ጀምራለች።

ቤተ መጻህፍቱ እንደማንኛውም ቤተ መጻህፍት ሁሉ በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉና ለህጻናትም ሆኑ ለአዋቂዎች የሚሆኑ በርካታ መጻህፍት በሀርድና ፎቶ ኮፒ ያሉት ቢሆንም አንድም ዓይነት ለኢትዮጵያውያን የሚሆኑ፣ ከኢትዮጵያውያን መግባቢያ ቋንቋዎች በአንዳቸው እንኳን የተጻፉ ተነባቢ መጻፍህት ግን እንደሌለው ይህች ኢትዮያጵዊት ታስተውላለች፣ ከዕለት ወደ ዕለትም ለምን እና እንዴት የሚሉ ጥያቄዎችን እያነሳች ማሰላሰልን ተያያዘችው። ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል ብላ ያመነችበትን የግል ሀሳቧን ይዛ በጉዳዩ ላይ ከአለቃዋ ጋር በመነጋገር በግሏ ከኢትዮጵያ መጻሕፍት ገዝታ ለማምጣት እንደምትሻ ሀሳቧን ታቀርብለታለች። አለቃዋም ሀሳቧን ተቀብሎ የከተማ አስተዳደሩ ግዢውን ለፈጽምላት እንደሚችል ቃሉን ይሰጣታል።

በዚሁም መሰረት በተደረገላት የገንዘብ ድጋፍ ግዢውና ማጓጓዣው ተሟልቶ የልጆች መጻህፍትን ከሀገር ቤት ካስመጣች በኋላ ለመጻህፍቱ ካታሎግ ሰርታ በላይብረሪው ውስጥ ከሌሎች ቋንቋዎች ጎን ለአገልግሎት እንዲቀርቡ በማድረግ የግል አሻራዋን አስቀምጣለች። ይህን ጅምር ሥራዋን ለማስፋት እንዲያስችላት ወደ ሀገር ቤት የምትጓዙ ወገኖቻችን በተለያዩ የሀገራችን ቋንቋዎች የተጻፉ የታሪክ፣ የባህልና የመሳሰሉ መጻህፍትን በማምጣት የበኩላችሁን ትብብር ብታደርጉላት ምኞቷና ምስጋናዋ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ሳንገልጽ አናልፍም።

እኛ የኢትዮጵያ ቀን በዓል አዘጋጆች ይህን ስራዋን በሰማንበት ወቅት በጅምር ሥራዋ ስለተደመምን እና ሁላችንም በየሥራ ቦታችን ለማህበረሰባችን ብሎም ለኢትዮጵያ ልናደርግ ለምንችለው በጎ ሥራ ታላቅ አስተማሪነት ይኖረዋል የሚል እምነት ስላሳደረብን በቅድሚያ የሥራ ቦታዋ ድረስ ሄደን ልንተዋወቃትና ሥራዋን ልናይላት ወስነን በቀጠሮ ተገናኘን።

የሰማነውን በዓይናችን አይተናል፣ ኮርተናልም። መጻህፍቱን በማንበብ የሚጠቀሙ ሕጻናት ከሌሉ ግን የተሰራው ሥራ ትርጉም አልባ ስለሚሆን ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ወደ ቬትዚኮን ቤተ መጻህፍት በመሄድ በሥራዋ እንዲያበረታቷት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን መግለጽ እንወዳለን።

በመጨረሻም እህታችን በግል ተነሳሽነት የሰራችው የጋራ እሴታችንን ከሌሎች ቋንቋዎችና ባህሎች ጋር በእኩል የማስቀመጡና ብሎም ከፍ የማድረጉ ሥራ በዚህ መድረክ ላይ ለኢትዮጵያ ቀን ቤተሰቦች መነገር ስላለበትና ለእያንዳንዳችንም የመልካም ሥራ ተምሳሌነቱ የላቀ በመሆኑ የኢትዮጵያ ቀን በ2025 በግለሰብ ካቴጎሪ የሚሰጠው እውቅና ለጋዜጠኛ ቅድስት በላይ እንዲሰጣት ወስኗል።

የኢትዮጵያ ቀን በግል እና በማህበር ለሀገር እና ለወገን የሚጥሩ ወገኖችን እያፈላለገ በየዓመቱ እውቅና ይሰጣል።

በዚህም አጋጣሚ እህታችንን ቅድስት በላይን በርቺ ፣ ከጎንሽ ነን በማለት ይህንን እውቅና ስንሰጥ እንደ ኢትዮጵያ
ቀን ቤተሰቦች ከፍ ያለ ክብርና ኩራት ይሰማናል።

.

Ethiopia Day In Swiss  is a non-political, non-profit, independent, community-based organization that is established to preserve and promote Ethiopian cultural heritage, thereby adding a positive impact to the host country – Switzerland.